የፕሬዝዳንቱ መልዕክት
የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች በቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 የከተማ አስተዳደሩ የዳኝነት አካል በመሆን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የከተማ ነክ ጉዳዮች ፍርድ ቤቶች በሚል በመጀመሪያና በይግባኝ ሰሚ ደረጃ የተቋቋሙ ሲሆን በኃላም በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና የአዲስ አበባ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በሚል በሁለት ደረጃ በድጋሚ ተዋቅረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች በህግ ተለይቶ በተሰጣቸው የፍትሐብሔር እና የወንጀል የመዳኘት ስልጣን የሚቀርብላቸው አቤቱታዎች ላይ አከራክረው ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ በፍርድ ቤቶቻችን የሚሰጡ የዳኝነት ውሳኔዎች ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ ለማድረግ የፍርድ ቤቶቻችን አመራሮች፣ ዳኞች እና መላው ሰራተኞች በቁርጠኝነት እየተጋን እንገኛለን፡፡ ይህንንም ከዳር ለማድረስ ፍርድ ቤቶቻችን ራዕይ እና ተልእኮ ለይተን አስቀምጠናል፡፡ በዚሁ መሰረት በ2022 ዓ.ም ፍ/ቤቶቻችን በአዲስ አበባ ከተማ የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ በህዝብ አመኔታ ያለው የዘመነ የዳኝነት አገልግሎት የሚሰጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት የሆነ ተቋም የመገንባት ራዕይ ሰንቀን እየሰራን እንገኛለን ፡፡ በቀጣይ አስር አመታት ለመድረስ ያስቀመጥነው ራዕይ እጅግ ትልቅ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ መዲና፣ የአለም አቀፍ ተቋማትና የፌዴራል መንግስት መቀመጫ እንዲሁም የኦሮሚያ ዋና ከተማ በመሆኑዋ ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ባህላዊ መስተጋብር ያለባት፣ ከሀገራችን ከተሞች አንፃር እጅግ ብዙ ነዋሪ ያላት በመሆኗ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ፍርድ ቤቶቻችን ከምን ጊዜውም በላይ ጠንካራ ተቋማት እንዲሆኑ ተግተን መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ከፈጣሪ በታች ፍትህ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው በፍ/ቤት የዳኝነት ውሳኔ ነው ተብሎ የሚታመን በመሆኑ በህዝባችን የተጣለብንን እምነት ሳናጓድል፣ ከሌብነትና ከአድሎ በፀዳ መልኩ ህግና ማስረጃን ብቻ መሰረት በማድረግ የምንሰጣቸው ውሳኔ የህግ የበላይነትን እና የሰው ልጆችን እኩልነት የሚያረጋግጥ እንዲሆን ለህሊናችን ተገዢ ሆነን ክቡር የሆነውን የዳኝነት ስራችንን እንድናከናውን ከአደራ ጭምር መልዕክቴን አስተላልፋለው፡፡ ከሰላምታ ጋር